Categories

A sample text widget

Etiam pulvinar consectetur dolor sed malesuada. Ut convallis euismod dolor nec pretium. Nunc ut tristique massa.

Nam sodales mi vitae dolor ullamcorper et vulputate enim accumsan. Morbi orci magna, tincidunt vitae molestie nec, molestie at mi. Nulla nulla lorem, suscipit in posuere in, interdum non magna.

ተተኪ ትውልድ ማፍራት

በዲያስፓራ ለምንኖር ኢትዮጵያን ከፊት የተቀመጠልን ትልቅ የቤት ሥራ ቢኖር ተተኪ ትውልድ ማፍራት ነው፡፡ በሀገር ቤት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የተሻለ ትውልድ መቅረጽ እንጂ ተተኪ ትውልድ ማፍራ አጀንዳቸው ላይሆን ይችላል፡፡ኢትዮጵያዊነት ፤ ማንነት ፤ ቋንቋ ፤ ባህል ፤ ሃይማኖትና ሥነ ምግባር በቀላሉ ከማኅበረሰቡ ተምሮ ማደግ የሚቻልበት ሀገር በመሆኑ፡፡ ከጎረቤት፤ ዘመድ አዝማድ፤ ጋደኛ ወዘተ የምንማራቸው የማንነታችን መሠረት የሆኑ ብዙ ዕሴቶች መኖራቸውን ሀገሬን ለቅቄ በባዕድ ሀገር መኖር ስጀምር ነው የተረዳሁት፡፡

 

በስደት ላለን ኢትዮጵያዊያን ልጅ ማሳደግ ቀላል እንዳልሆነ መናገር ለቀባሪው አረዱት አይነት ነገር ሊሆን ይችላል፡፡ ልጆቼን እይልኝ ገበያ ደርሼ እመጣለሁ ከሚባልበት ሃገር መኪና ስር ቁጭ አድርጎ ዕቃ ማቀበል ወደማይቻልበት ሀገር መምጣት እንዴት አስቸጋሪ አይሁን፡፡ በሀገራችን ኢትዮጵያ እኛ ተጨንቀን ለልጆቻችን የማናደርግላቸው እነርሱ ግን አብረዋቸው ከሚያድጉ ሕጻናት ፤ ከቤተሰባቸው ፤ ከጎረቤት ወዘተ የሚማሩት ብዙ ቁም ነገር አለ፡፡ ምን አልባት ልጁ እንዴት ቋንቋ እንደተማረ የማያውቅ ብዙ አባት ይኖራል፡፡ በውጪው ሀገር ግን ይህ ዕድል በቀላሉ የለም ፤ እያንዳንዱን ነገር ከቤተሰብ አሊያም ከቴሌቪዥን መስኮት ነው የሚማሩት፡፡

 

እንግዲህ ጊዜ የሌለው 16 ሰዓት የሚሠራ ወላጅ ሲሆን ደግሞ ሙሉ በሙሉ ከቴሌቪዥን ወይም ከሚያድጉባቸው ዴይ ኬሮች ይሆናል ማለት ነው፡፡ ወልደው ለባዳ ይላሉ ይሔ ነው፡፡ ከልጅነታቸው ጀምሮ በፈረንጆቹ ቋንቋ አድገው በባህላቸው ተውጠው የሚያድጉ ኢትዮጵያዊያን ልጆችን ቤት ይቁጠራቸው፡፡ እንግሊዘኛ ቋንቋ ብቻ መናገሩን እንደ ሥልጣኔ የሚመለከት ወላጅም ሞልቷል፡፡ ልጆች የእንግሊዘኛውን ቋንቋ መማሪያ ጥሩ መንገድ እንደሆኑ አድርጎ የሀገሩን ቋንቋ ወንዝ አያሻግርም ያለም ቀላል አይደልም፡፡ እንግዲህ ከቋንቋው ጋር ባህል እና ሃይማኖትም እንዲሁም ኢትዮጵያዊነት አብረው ይዘነጋሉ፡፡

 

ኢትዮጵያዊያን በስደት ዓለም ወጥተን ኑሮ መሥርተን መኖር ከጀመርን ገና ግማሽ ክፍለ ዘመን የማይሞላ ቢሆንም ውጪ ተወልደው ማንነታቸውን የጠበቁ ጥቂት ማግኘት ግን ከባድ ነው፡፡ የሰው ልጅ መሠረታዊ የሆኑ ፍላጎቶቹን ምግብ ፤ ልብስ መጠለያ ሲያማላ ፤ ተምሮ ያለመውን ሲያገኝ ፤ ሠርቶ በቂ ገንዘብ አለኝ ሲል በአይምሮው የሚመጣ ትልቅ ጥያቄ ቢኖር ማንነት ነው፡፡ ከየት እንዴት መጣሁ መሠረቴ ምንደር ነው? ብሎ ማንነቱን ማጉላት ለመሠረታዊ ስኬት ወይም እርካታ ትልቅ ምንጭ ነው፡፡ ለነገሩ ተምሮም ፤ ነግዶም ፤ ሠርቶም ስኬታማ ለመሆን ማንነት ትልቅ ድርሻ አለው፡፡ ለዚህ ነው የሰው ጌጥ አያደምቅ የሚለው የሀገሬ ሰው፡፡

 

በማንነት ሚዛን ሲመዘን አንድ ትውልድ እንኳን ለመተካት የቸገረው ኢትዮጵያዊ እንመለከታለን፡፡ በኑሮ ጫና ፤ በባህል ግጭት የተጠመደው ወገኔ የቱን ይዞ የቱን እንደሚተው ግራ እየገባው የወለዳቸው ልጆቹ የእርሱ እስከማይመስሉ ድረስ ከእጁ ሲያመልጡ መመልከት አዲስ አይደለም፡፡ በአጠቃላይ ተተኪ ትውልድ ማፍራት እጅግ አስቸጋር እንደሆነብን መረዳት ይቻላል፡፡

 

በአንጻሩ እጅግ ብዙ ዓመታትን በስደት ያሳለፉ ሕንዶች እና እስራኤላዊያን ቋንቋ ፤ ባህል ፤ ሃይማኖት እና ሥርዓታቸውን ጠብቀው በመቆየታቸው እንደ ወግ አጥባቂ ሲቀለድባቸው እንመለከታለን፡፡ እነዚህ ሕዝቦች በስደት ዓለም እጅግ ስኬታማ ከሚባሉት ወገኖች ሲሆኑ ፤  ለተሰደዱበት ሀገርም ሆነ ለሀገራቸው እጅግ በጣም ትልቅ ጥቀም ሲያበረክቱ እንመለከታለን፡፡ ከእነዚህ ጋር ቻይናዎች እና እስፓኒሾችም ጠንከር ያለ ማንነታቸውን የመጠበቅ ሃላፊነት ሲወጡ እንመለከታለን፡፡ ምነው አንገት ቀና የሚያደርግ ታሪክ ፤ መንግስተ ሠማይ የሚያስገባ ሃይማኖት ፤ እጅግ የተዋበ ባህል እና ሥርዓት ያለን እኛ ማንነታችንን ጣል አደረግነው? መልሱን ለእናንተ መወያያ ትቼዋለሁ፡፡

 

ዛሬ ዛሬ በሔዱበት ቦታ ሁሉ ከኮምፒውተር ጌም እንጂ ከሰው የማያወሩ ታደጊ ልጆች መመልከት አዲስ አይደለም፡፡ እንደ ጥቁሮቹ በቀኝ ሳይገዛ ሱሪውን አዝረክርኮ የሚሔድ የአበሻ ቲኔጅ ማየት በጣም የተለመደ ነው፡፡  ይባስ ብሎ እንደ እስፓኒሽ እና ጥቁር ወጣቶች የአበሻ ጋንግስተር ግሩፕ እየተፈለፈለ መሆኑም ጆሮን ጭው የሚያደርግ ዜና ከሞሆን አልፏል፡፡ ታዲያ ተተኪ ኢትዮጵያዊ የቱ ጋር ነው ያለው? እንወያይበት

 

በሌላ ጊዜ ለምን ማንነታችንን ጣልነው? ለመመለስ እና ተተኪ ትውልድ ለማፍራት ምን እናድርግ በሚል ክፍል ሁለት መጣጥፍ እመለሳለሁ፤፤

 

ዘሚካኤል

Categories

A sample text widget

Etiam pulvinar consectetur dolor sed malesuada. Ut convallis euismod dolor nec pretium. Nunc ut tristique massa.

Nam sodales mi vitae dolor ullamcorper et vulputate enim accumsan. Morbi orci magna, tincidunt vitae molestie nec, molestie at mi. Nulla nulla lorem, suscipit in posuere in, interdum non magna.