Categories

A sample text widget

Etiam pulvinar consectetur dolor sed malesuada. Ut convallis euismod dolor nec pretium. Nunc ut tristique massa.

Nam sodales mi vitae dolor ullamcorper et vulputate enim accumsan. Morbi orci magna, tincidunt vitae molestie nec, molestie at mi. Nulla nulla lorem, suscipit in posuere in, interdum non magna.

የድምጻዊ ሃጫሉ ግድያ የቀሰቀሰው ውጥረት የጸጥታ ስጋት ጋርጧል

ታዋቂው የአፋን ኦሮሞ ድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ትናንት ምሽት ማንነታቸው ባልተወቁ ሰዎች አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በጥይት ተመትቶ ሕይወቱ አልፏል። ይህ ዜና የቀሰቀሰው ቁጣ በተለይ በኦሮሚያ ክልል እና በአዲስ አበባ ከተማ የጸጥታ ስጋት ፈጥሯል።

ሃጫሉ ሁንዴሳ (ፎቶ፣ ከኦቢኤን ቃለመጠይቅ)

ውጥረቱን ተከትሎ ዛሬ ጠዋት ኢንተርኔት ተቋርጦ ነበር። እኩለ ቀን ገደማ ተመልሶ መከፈቱ ታውቋል። በሌላ በኩል የፌደራል ፖሊስ የኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክን ቢሮ በመያዝ የተወሰኑ ጋዜጠኞች መታሰራቸውን ጣቢያው በማኅበራዊ መገናኛ አስታውቋል።

ዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ዛሬ ከማለዳ ጀምሮ ከወትሮ በመጠኑ የቀዘቀዘ እንቅስቃሴ ሲታይባት ውሏል። ሆኖም ይህን ዘገባ በምናጠናቅርበት ወቅት ይህ ነው የሚባል ከፍተኛ የጸጥታ ችግር ስለመፈጠሩ አልተዘገበም። ቢሆንም ውጥረቱ በጊዜ ካልረገበ አደገኛ የጸጥታና የመረጋጋት ጅግር ሊያስከት እንደሚችል በመንግሥት ውስጥ ያሉ ባለሞያዎች ሳይቀሩ ስጋታቸውን እየገለጹ መሆኑን ዋዜማ ተረድታለች። ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የመንግሥት ሐላፊዎች ተከታታይ መግለጫ እንደሚሰጡ እንደሚጠበቅ ተረድተናል።

ትናንት ምሽት የሃጫሉ ሞት ከተሰማ ብዙም ሳይቆይ የከተማዋ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ለኢቢሲ በሰጡት መግለጫ “የተወሰኑ ተጠርጣሪዎች” መያዛቸውንና ምርመራው መጀመሩን ገልጸው ነበር። የኮሚሽነሩ መግለጫ መረጃ ከመስጠት ይልቅ ሕዝቡን በማረጋጋት ላይ ያተኮረ ነበር።

በአቃቂ ቃሊት ክፍለ ከተማ፣ ገላን ኮንዶሚኒየም በሚባልው አካባቢ ከምሽቱ 3፡30 ገደማ ተፈጸመ በተባለው ጥቃት በጥይት የተመታው ሃጫሉ በአቅራቢያው ወደነበረ ሆስፒታል ቢወሰደም ሕይወቱን ማትረፍ ሳይቻል ቀርቷል። ፖሊስም ሆነ የሆስፒታል ምንጮች ሃጫሉ በስንት ጥይቶች እንደተመታና ምን አይነት ጉዳይ ለሞት እንዳበቃው አልገለጹም።

አስከሬኑ ከጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል ወጥቶ ሌሊቱን ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ለአስከሬን ምርመራ መወሰዱን ሰምተናል። ዛሬ ማክሰኞ ረፋድ ላይም እጅግ በርካታ የድምጻዊ አድናቂዎች በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል አቅራቢያ በሚገኙት ጎዳናዎች ተሰብስበው ሀዘናቸውንና አድናቆታቸው በስሜት ሲገልጹ አርፍደዋል። አስቀድሞ አስከሬኑ የሃጫሉ የትውልድ ቦታ ወደ ሆነችው ወደ አምቦ ከተማ ይወሰዳል በሚል ጉዞ ቢጀመረም በመካከል የሐሳብ ለውጥ ተደርጎ አዲስ አበባ ወደሚገኘው የኦሮሞ የባህል መዕከል እንደተወሰደ ተገልጻል።

ይህን ዘገባ እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ የድምጻዊ ቀብር የት እንደሚፈጸም ቁርጥ ያለ ውሳኔ አለመሰጠቱን አውቀናል። ውሳኔውን የሚሰጡት አካሎች ማንነትም ግልጽ አይደለም። አንድ ከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ሃላፊ፣ የሃጫሉ ቀብር ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካና የደኅንነት አንደምታ ያለው ጉዳይ በመሆኑ “የመንግሥት አካላት ከትናንት ምሽት ጀምሮ በጥብቅ እየተነጋገሩበት” መሆኑን እኩለ ቀን ገደማ ለዋዜማ አረጋግጠዋል። በሌላ በኩል፣ ተሰሚነት ያላቸው የኦሮሞ ፖለቲካ መሪዎችና አክቲቪስቶች ቀብሩ በአዲስ አበባ እንዲፈጸም ፍላጎት እንዳላቸው ያሰባሰብናቸው አስተያየቶች ይጠቁማሉ።

የድምጻዊው ሞት ከተሰማ በኋላ በማኅበራዊና በመደበኛ ሚዲያ (ዩ ትዩብን ጨምሮ) በርካቶች ልባዊ ሐዘናቸውን እየገለጹ ነው። ሆኖም በቁጭትና በእልህ ስሜት የሚቀርቡት ስሜት ቆስቋሽ አስተያየቶች አመጽ ሊጋብዙ እንደሚችሉ ታዛቢዎች እያስጠነቀቁ ነው። የጸጥታ መሥሪያ ቤቱ በበኩሉ ሁኔታው የደኅንነት አደጋ ሊጋብዝ እንደሚችል በማመን ከወትሮው ለየት ያለ ክትትል ሲያደርግ ማደሩን ሰምተናል።

ዛሬ ከጠዋት ጀምሮ ጠቅላይ ሚኒስትሩንና የኦሮሚያ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳድርን ጨምሮ በርከት ያሉ ከፍተኛ የመንግሥት መሪዎች ሀዘናቸውን ሲገልጹ፣ ገዳዮች ለሕግ እንደሚቀርቡ ሲያሳስቡ፣ ሕዝቡ እንዲረጋጋ ሲማጸኑ ቢያረፍዱም በተለይ በኦሮሚያ ክልል ሰልፎችንና ተቃውሞዎችን ማስቀረት አልቻሉም። በአዲስ አበባ አስከሬኑ ሲሸኝ በነበርበት አካባቢ በጸጥታ ኅይሉና በሰልፈኖቹ መካከል በተፈጠር አለመግባባት ፖሊስ አስለቃሽ ጭስ መጠቀሙ ተዘግቧል። በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ ከተሞች ወጣቶች የተቃውሞ ድምጻቸውን እያሰሙና በመንግሥት ተቋማት ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን፣ በመንግሥት ሃይሎች ተፈጸመ በተባለ ምላሽም ሁለት ሰዎች ጭሮ ላይ መሞታቸውን ቢቢሲ ኦሮሚኛ ዘግቧል። በሐረር ከተማ የሚገኘው የራስ መኮንን ሐውልት በተቃዋሚዎች መፍረሱን የሚያሳዩ ፎቶዎች በማኅበራዊ ሚዲያ እየተሰራጩ ነው።

ሃጫሉ ሁንዴሳ በኦሮሞ ሙዚቃ በተለይም ለአዲሱ ለውጥ ቁልፍ ሚና በነበረው የኦሮሞ ወጣቶች ተቃውሞ ወቅት እጅግ ገኖ የወጣ ድምጻዊና የዘፈን ግጥም ጸሐፊ ነው። በዘመኑ “የኦሮሞ ወጣቶችን የትግል ስሜትና የዴሞክራሲ ፍላጎት የእርሱን ያህል አጉልቶ ያወጣና በጥበበ የገለጸ የጥበብ ሰው ማግኘየት አይቻልም” ብለውናል አንድ አድናቂው። የሃጫሉ የሙዚቃ ሥራዎችና የትግል መልዕክቶች ከኦሮሞ ወጣቶች ባሻገርም አድናቆትን ያስገኙለት ነበሩ።

—–
የዋዜማ ሬዲዮ ባልደረቦች በሃጫሉ ሁንዴሳ ሞት የተሰማንን ሀዘን እንገልጻለን። ለቤተሰቦቹና ለወዳጅ አድናቂዎቹም መጽናናትን እንመኛለን።

The post የድምጻዊ ሃጫሉ ግድያ የቀሰቀሰው ውጥረት የጸጥታ ስጋት ጋርጧል appeared first on Wazemaradio.

Source:: http://wazemaradio.com/%E1%8B%A8%E1%8B%B5%E1%88%9D%E1%8C%BB%E1%8B%8A-%E1%88%83%E1%8C%AB%E1%88%89-%E1%8C%8D%E1%8B%B5%E1%8B%AB-%E1%8B%A8%E1%89%80%E1%88%B0%E1%89%80%E1%88%B0%E1%8B%8D-%E1%8B%8D%E1%8C%A5%E1%88%A8%E1%89%B5/

Categories

A sample text widget

Etiam pulvinar consectetur dolor sed malesuada. Ut convallis euismod dolor nec pretium. Nunc ut tristique massa.

Nam sodales mi vitae dolor ullamcorper et vulputate enim accumsan. Morbi orci magna, tincidunt vitae molestie nec, molestie at mi. Nulla nulla lorem, suscipit in posuere in, interdum non magna.