Categories

A sample text widget

Etiam pulvinar consectetur dolor sed malesuada. Ut convallis euismod dolor nec pretium. Nunc ut tristique massa.

Nam sodales mi vitae dolor ullamcorper et vulputate enim accumsan. Morbi orci magna, tincidunt vitae molestie nec, molestie at mi. Nulla nulla lorem, suscipit in posuere in, interdum non magna.

ስለ ተሐድሶ ኑፋቄ ..... በወጣትነት ለቀሪ ዕድሜ ሁሉ የሚተርፍ የተሳሳተ ውሳኔ ስለሚወስኑ ሰዎች ....

ስለ ተሐድሶ ኑፋቄ ….. በወጣትነት ለቀሪ ዕድሜ ሁሉ የሚተርፍ የተሳሳተ ውሳኔ ስለሚወስኑ ሰዎች ….

————————–

++ ተሐድሶ ውስጥ የሚገቡ ወጣት ልጆች መዘዙን አልተረዱም ገና፤

++ የዕውቀትም የዕድሜም ውሱንነት ወደ ተሳሳተ መንገድ ያደርሳል፤

++ ውሳኔህን መለስ ብለህ ተመልከት፤

++ “እልህ ሃይማኖት ይሆናል» ነውና በእልህ የተሳሳተ መንገድ አትከተል፤

———————-

በየፌስቡኩ “ተሐድሶ ነን» ብለው ያወጁ ብዙ ሰዎችን ስመለከት ለጋ ዕድሜያቸው ከፊታቸው ላይ የሚነበብ ወጣቶች መሆናቸውን አየኹ። በርግጥ የሚያሰማሯቸው በክፋት ያረጁ ሰዎች መሆናቸውን አውቃለኹ። “ተሐድሶ ሁሉ ወጣት ነው» ማለቴ እንዳልሆነ በደንብ ተረዱልኝ። ስለ ተሐድሶ እና ስለ ተልዕኳቸው ላለፉት 20 ዓመታት በደንብ ጠንቅቄ አውቃለኹ። ገና “ተሐድሶ መናፍቃን» የሚባለው ቃል ሳይታወቅና ምንነታቸው ገና ምሥጢር ከነበረበት ዘመን ጀምሮ ብዙ ውጣ ውረድ አሳልፈናል። የምናገረው ከዚያን ዘመን ጀምሮ ስለማውቃቸው ጥፍራቸው የዘረዘረ፣ ቀንዳቸው የከረከረ ተሐድሶዎች ሳይሆን ገና በለጋ ዕድሜ ላይ ስላሉት እና በጥቃቅን ነገር ስለተደለሉት ስለ ወጣቶቹ ነው።

————-

ወጣትነት የዋህና አስቸጋሪ ዕድሜ ነው። በእግዚአብሔር ቸርነት ቀና ቀናውን መንገድ ለመሔድ ካልተቻለ በስተቀር በቀላሉ ሕይወት ሊበላሽየሚችለበት “የሁሉን አውቃለሁ» ባይነት ቅራኝነት ያለበት ዘመን ነው። ከሃይማኖት አንጻር ያለውን ብቻ ነው የማነሣው።

በወጣትነት ከዕውቀት እጅግ ጥቂቱን ከማወቃችንም በላይ በተለይ ከሃይማኖት ዕውቀት ደግሞ እጅግ ኢምንቱን ነው የምንረዳው። ባልረጋ እና እሳት በሆነ የወጣትነት ሰውነት ዕውቀት መንፈሳዊ ለማደርና ለመኖር ብዙ ትቸገራለች። በዚያ ላይ የአውቃለኹ ባይነት እሳት ስናነድድባት ደግሞ ሕይወታች በድንቁርና ጨለማ የተዋጠች ትሆንና እኛ ግን በብርሃን የተሞላን እንዲመስለን ታደርገናለች።

ከዚህ ዓይነቱ አጋጣሚ አንዱ ደግሞ በቅጡ ስላልተረዳናት ቤተ ክርስቲያነችን እና በቅጡ ስለማናውቀው ባህላችን የምንወስደው ፈጣን ድምዳሜ እና የምንሄደው የተሳሳተ መንገድ ነው። ወዳጄ ዲ/ን ዳንኤል ክብረት የሚላት አንዲት ጥሩ አባባል አስታውሳለኹ። “መቸም ከዚህ በፊት የነበሩ አባቶቻችን በሙሉ ያልተገለጠላቸው አዲስ ዕውቀት እና አዲስ መንፈሳዊ ጥበብ በዚህ ዘመን ለእኛ አይገለጥም» የምትል። ቃል በቃል በትክክል ማስታወሴን እንጃ። ሐሳቡን ከተረዳችሁልኝ ይበቃል። (ራሱ ዳንኤል ይጨምርበት)

እንግዲያማ፤ ከቤተ ክርስቲያን ትምህርት ወጥተው በፕሮቴስታንት መሠረተ እምነት የተቃኘ ኦርቶዶክሳዊነት ለሚፈልጉ ሰዎች “በርግጥ እኒያ ሁሉ ቅዱሳን አባቶቻችን እና ቅዱሳት እናቶቻችን ያልተገለጸላቸው አዲስ ዕውቀት» አገኘን ብለው ሲያስቡ መሳሳታቸውን ሊረዱ ይችላሉ። ሌላ ማስረጃም አያሻቸው። እንግዲህ መንገድን መመርመር ነው።

————-

“እልህ ሃይማኖት ይሆናል» እንደሚባለው በእልህ ከያዙት የማይመለሱ ብዙ ሰዎች አሉ። መንገዳቸው የተሳሳተ መሆኑን ያወቁ ሰዎች ቢመለሱ ለእነርሱ ሽንፈት አይደለም። እንዲያውም ከእግዚአብሔር ትልቅ ዋጋ ያገኙበታል። “ተሳስቼ ነበር» ማለት ደካማነት አይደለም። ደካማነት የሚሆነወ በዓለም ሚዛን ለሚመስኑን ሰዎች ብቻ ወን። በእግዚአብሔር ሚዛን ግን ጠንካራነት ነው። ዕድሜ ለንስሐ፤ ዘመን ለፍስሐ የሚሰጥ አምላክ በመሳሳታችን ሳይሆን በመመለሳችን እጅግ ይደሰታል። “የሰማይ መላእክት» ጭምር ደስ ይሰኛሉ። ወንጌል እንዳስተማረችን በየሉቃስ ወንጌል 15፥7 “እላችኋለሁ፥ እንዲሁ ንስሐ ከማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኝ ጻድቃን ይልቅ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በሰማይ ደስታ ይሆናል።» እንዲሁም በምዕ. 15፥10 “እላችኋለሁ፥ እንዲሁ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ደስታ ይሆናል።» መላእክት ጭምር የሚደሰቱበት ተግባር ጥፋትን እና ኃጢአትን ማመን ከሆነ ማመኑ ያስከብራል እንጂ አያስነቅፍም።

ይሁን እንጂ ከዚህ የተሐድሶ መንገድ የሚመለሱ ሰዎች በቀላሉ እንዲመለሱ “የማርያም መንገድ» ማዘጋጀት ይገባናል። ተመልሻለኹ ስላለ ተመልሷል ማለት ሳይሆን የተሳሳተውን ነገር አቅርቦ ትክክለኛውን ትምህርት ማግኘቱን ማረጋገጥ፣ ከተመረዘው የኑፋቄ ትምህርት ወጥቶ ርቱዕ የሆነችውን ትምህርት ማግኘቱን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። መጀረሚያም የወሰደው የተሳሳተ ትምህርት ከሆነ ሲመለስ ደግሞ የተስተካከለ ትምህርት ማግኘት አለበት። ገና ለገና ተመልሷል ብሎ ዐውደ ምህረት ለዐውደ ምሕረት “መስክር» እያሉ ማቆም ከበፊቱ የባሰ ጥፋት ያመጣል።

———

በ1980ዎቹ እና 90ዎቹ “ምስክርነት» በሚባል ፋሽን መሰል የዐውደ ምሕረት ዝግጅት ከሌላ እምነት የመጡ ሰዎች እንዲናገሩ ይደረጉ ነበር። ሰዎቹ ለምን እንደመጡ ሳያውቁ፣ ትክክለኛውን ትምህርት ሳይማሩ፣ ብቻ “መስክር» እየተባሉ ቁጥር አንድ ሰባኪዎች ሆነው ነበር። የሚሰማቸው ሕዝብ እኮ በእምነቱ ያለ ሕዝብ ነው። እነርሱ ናቸው አዲሶቹ። ማነው ለማን የሚነግረው?

—–

አሁንም ቢሆን ሊመለሱ ለሚፈልጉ ሰዎች ትምህርት መስጫ መንገድ መመቻቸት አለበት። ከዕጽ ሱስ ለሚመለሱ፣ ከተለያየ አደጋ ለሚያገግሙ ሰዎች “የማገገሚያ ቦታ፣ Rehabilitation) እንደሚዘጋጀው ሁሉ ከኑፋቄ ድቀት እና ስብራት ለመጠገን ለሚመለሱ ሰዎች ከዚያ ስብራታቸው የሚድኑበት ትምህርትና ሕክምና የሚሰጥበት ቦታ መዘጋጀት አለበት። መምህራን ይህንን ማሰብ አለባቸው። ማጋለጡ ብቻ ዘላቂ መፍትሔ አያመጣም።

—–

አሁን ጥሪዬ ገና በለጋ ዕድሜያቸው ዘማሪ፣ ሰባኪ ተብለው በፋሺንም መልክ ይሁን በጓደኛ ጉትጎታ ለ”አገልግሎት» ብለው ሳያውቁት የቤተ ክርስቲያን ጠላት ለሆኑት ልጆች ነው። አሁን በለጋነታችሁ የወሰናችሁት ውሳኔ በዕውቀትም በዕድሜም ስትጎለምሱ፣ ከሁሉም በላይ በእግዚአብሔር ቸርነት በቃሉ ወተት ስታድጉ የምትፀፀቱበት ስለሚሆን አሁን መንገዳችሁን ቆም ብላችሁ ተመልከቱ። ራሳችሁን ለመመልከት እንዳትችሉ ያላችሁበት ማዕበል ፋታ ስለማይሰጣችሁ ለጻድቁ ኢዮብ እንደተባለው “ይህን ስማ፣ ቁም፥ የእግዚአብሔርንም ተአምራት አስብ።» (ኢዮብ 37፥14)። ከዚያ ጊዜ በራሱ ስሕተታችሁን ያሳያችኋል።

———-

Source:: http://www.adebabay.com/2017/07/blog-post_31.html

Categories

A sample text widget

Etiam pulvinar consectetur dolor sed malesuada. Ut convallis euismod dolor nec pretium. Nunc ut tristique massa.

Nam sodales mi vitae dolor ullamcorper et vulputate enim accumsan. Morbi orci magna, tincidunt vitae molestie nec, molestie at mi. Nulla nulla lorem, suscipit in posuere in, interdum non magna.