Categories

A sample text widget

Etiam pulvinar consectetur dolor sed malesuada. Ut convallis euismod dolor nec pretium. Nunc ut tristique massa.

Nam sodales mi vitae dolor ullamcorper et vulputate enim accumsan. Morbi orci magna, tincidunt vitae molestie nec, molestie at mi. Nulla nulla lorem, suscipit in posuere in, interdum non magna.

ኦነግ ሸኔ አዲስ ዘመቻ ጀምሯልን?

ዋዜማ- ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን፣ ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ዞኖች ከመንግሥት ወታደሮች ጋር ከወትሮው በተለየ መልኩ ተከታታይ ውጊያ እያካሄደ ስለመሆኑ ዋዜማ ከተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች  ካሉት ምንጮቿ ካሰባሰበችው መረጃ መረዳት ችላለች። መረጃዎቹንም፣ ከክልሉ አካባቢዎች አኳያ እንደሚከተለው አሰባጥረናቸዋል።

     ወለጋ

አማጺ ቡድኑ በቄለም ወለጋ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች ከመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ጋር እያደረገ ባለው ውጊያ ነዋሪዎች፣ ‘አጣብቂኝ ውስጥ ገብተናል’ ሲሉ ለዋዜማ ተናግረዋል። ቡድኑ በተለይም ዳሌ ዋበራ፣ ጊዳሚ ሃዋ ገላን እና ሰዮን በመሳሰሉ ወረዳዎች ገጠራማ አካባቢዎች፣ ከመንግሥት ኃይሎች ጋር ከፍተኛ ውጊያ በማድረግ ላይ እንደሆነ ዋዜማ ተረድታለች።

 በሁለቱ ኃይሎች መካከል የሚደረገው ውጊያ በተለይም ካለፈው ሳምንት ሰኞ ጀምሮ ተጠናክሮ የቀጠለ መሆኑን የገለጹት ነዋሪዎች፣ ከቤት መውጣትም ሆነ ማኅበራዊ ሕይወታቸውን መከወን እንዳልቻሉ አውስተዋል። ውጊያው በተለይም የመከላከያ ሠራዊት ካምፕ ባለበት ሰዮ ወረዳ አካባቢ በስፋት እየተካሄደ ስለመሆኑም ሰምተናል። ውጊያው ከመጀመሩ ቀደም ብሎ በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባላት በኩል ለሕዝቡ ‘ምንም አይነት እንቅስቃሴ እንዳታደርጉ’ የሚል መልዕክት ተላልፎ እንደነበርም ዋዜማ የደረሳት መረጃ ያመለክታል።

በምስራቅ ወለጋ ዞንም፣ ታጣቂው ቡድን ከመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ጋር ውጊያ እያደረገ መሆኑን ዋዜማ ከምንጮቿ ሰምታለች። ውጊያው እየተካሄደ ካለባቸው የዞኑ አካባቢዎች መካከል ቢሎ ቦሼ፣ ሌቃ ዱለቻ እና ኑኑ ቁምባስን የመሳሰሉ ወረዳዎች እንደሚገኙበትም ነዋሪዎች ለዋዜማ አስረድተዋል። በተለይም በዞኑ የመከላከያ ሠራዊት ካምፕ ባለባቸው ጅማቴ እና አዳሚንን በመሳሰሉ አካባቢዎች በሁለቱ ኃይሎች መካከል ከፍተኛ ውጊያ መካሄዱን ነዋሪዎች ገልጸዋል።

እነዚህ ወረዳዎች ቀድሞውንም ከፍተኛ የሆነ የጸጥታ ችግር ያለባቸው እና የታጣቂ ቡድኑ አባላት በስፋት የሚንቀሳቀሱበት እንደሆኑ የገለጹት ምንጮች፣ ‘አሁን ያለው ሁኔታ ከወትሮው የተለየና ለነዋሪው እጅግ ፈታኝ እየሆነ ነው’ ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ‘የአማጺ ቡድኑን አባላት ትሸሽጋላችሁ’ በሚል፤ ከታጣቂው ቡድን በኩል ደግሞ ‘የመንግሥት ወታደሮችን ታግዛላችሁ’ በሚል ከሁለት ወገን በሚመጣ ጫና የተነሳ ‘አጣብቂኝ ውስጥ ገብተናል’ ሲሉ ነዋሪዎቹ የሁኔታውን አስቸጋሪነት ለዋዜማ ገልጸዋል።

          ሸዋ

  በክልሉ ምዕራብ ሸዋ ዞን ግንደበረት ወረዳ በሁለቱ ኃይሎች መካከል እሁድ ግንቦት 25 እና ሰኞ ግንቦት 26 2016 ዓ.ም. ከፍተኛ የሆነ ውጊያ ሲደረግ እንደነበር ዋዜማ በአካባቢዎቹ ካሏት ምንጮች ተረድታለች። በዕለቱም በርካታ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዝግ እንደነበሩ ነዋሪዎቹ አስረድተዋል። በተለይም በወረዳው ደርጌ በተባለ ቀበሌ ከፍተኛ ውጊያ ሲካሄድ መቆየቱን ያስረዱት ምንጮች፣ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ አካባቢውን የመከላከያ ሠራዊት አባላት እንደተቆጣጠሩት አስረድተዋል። በተመሳሳይ በዞኑ ጀልዱ ወረዳ ቀርሳ ማርቲ ቀበሌ፣ ሰኞ ግንቦት 26 2016 ዓ.ም. በሁለቱ ኃይሎች መካከል ውጊያ እንደነበር ምንጮች አስረድተዋል። ‘አሁን ላይ አንጻራዊ ሰላም አለ’ የሚሉት ነዋሪዎች፣ ‘ነገር ግን፣ መቼ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ስለማናውቅ ስጋት ላይ ነን ሲሉ’ ስጋታቸውን አጋርተውናል። 

 በምስራቅ ሸዋ ዞን ዱግዳ ወረዳ እና በመቂ ከተማ ወልዳ ቀሉና በተባለ ቀበሌም በተመሳሳይ ውጊያ ሲደረግ እንደሰነበተ ዋዜማ ተረድታለች።

 በክልሉ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን የተለያዩ ወረዳዎችም ተመሳሳይ ግጭት እየተካሄደ መሆኑን ዋዜማ ከአካባቢው ነዋሪዎች ሰምታለች። ለአብነትም በዞኑ አደአ በርጋ ወረዳ ገጠራማ ቀበሌዎች ከፍተኛ የሆነ ግጭት በሁለቱ ኃይሎች መካክል እየተካሄደ ስለመሆኑ ሰምተናል። በተጨማሪም ከሰኔ 2 2016 ዓ.ም. ወዲህ፣ በዞኑ ቀርሳ ማሊማ ወረዳ ጌቶ እና ጂማታ በተባሉ ቀበሌዎች በሁለቱ ኃይሎች መካከል በተካሄደ ውጊያ ንጹሃን መሞታቸውን እና መቁሰላቸውን ነዋሪዎች  አስረድተዋል። ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችም ሌመን ሆስፒታል ገብተው የሕክምና እርዳታ እያገኙ እንደሆነ ዋዜማ የደረሳት መረጃ ይጠቁማል። በተጨማሪም ቶሌ፣ ሰዴን ሶዶ፣ በቾ፣ ደዎና ሰበታ አዋስን በመሳሰሉት ወረዳዎች ባሉት ገጠራማ አካባቢዎች አልፎ አልፎ ግጭቶች መኖራቸውንም አውስተዋል።

  በአደአ በርጋ ወረዳም የመከላከያ ሠራዊት መገልገያ የሆኑ ሦስት ተሽከርካሪዎች በታጣቂ ቡድኑ ተቃጥለው ከጥቅም ውጪ መሆናቸውን የዐይን እማኞች ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪ በአማጺ ቡድኑ በኩል፣ የአርሶ አደሩን እንሰሳት መንዳትና አርዶ መብላትን የመሳሰሉ ድርጊቶች በተደጋጋሚ እየተፈጸሙ ስለመሆኑ ነዋሪዎች ለዋዜማ ነግረዋታል።

  በሰሜን ሸዋ ዞን የተለያዩ ወረዳዎችም እንዲሁ በመንግሥት ወታደሮች እና በታጣቂው ቡድን አባላት መካክል ግጭት እየተካሄደ ስለመሆኑ ዋዜማ የደረሳት መረጃ ያመለክታል። ከግጭቱ ጋር ተያይዞ በዞኑ ግራር ጃርሶ ወረዳ ባለፈው እሁድ ግንቦት 25 2016 ዓ.ም. ከ 20 በላይ ንጹሃን ዜጎች በአማጺ ቡድኑ ታጣቂዎች በተፈጸመባቸው ‘ማንነት ተኮር ነው’ በተባለ ጥቃት ሕይወታቸው ማለፉን ምንጮች ለዋዜማ አረጋግጠዋል። በተመሳሳይ በዞኑ ዋጫሌ ወረዳ በቾ ፋሌኒ በተባለ ቀበሌ፣ 3 ንጹሃን መገደላቸውን እና በርካታ ቤቶች መቃጠላቸውን ምንጮች ጠቁመዋል። በዞኑ ካለው አስከፊ የጸጥታ ችግር የተነሳ አምቡላንስን ጨምሮ ማንኛውም የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ከምሽቱ 12 ሰዓት በኋላ መታገዱን የገለጹት ምንጮች፣ በዚህ ሁኔታ ውስጥ መኖር ከጀመሩ አንድ ዓመት እንዳለፋቸው ለዋዜማ ተናግረዋል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ በዞኑ ዋጫሌ ወረዳ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች 29 ሰዎችን አፍነው መውሰዳቸውን ዋዜማ ከምንጮቿ ሰምታለች። አማጺ ቡድኑ ድርጊቱን የፈጸውመው እሁድ ሰኔ 2 2016 ዓ.ም. ከቀኑ 11 ሰዓት አካባቢ ሙከጡሪ ከተማ መግቢያ ላይ ልዩ ስሙ ጃቴ በተባለ ስፍራ እንደሆነ ታውቋል። ታፍነው የተወሰዱት ሰዎች መነሻቸውን አዲስ አበባ ባደረጉ ሁለት በተለምዶ አባዱላ ተብለው በሚጠሩ ተሽከርካሪዎች የተሳፈሩ፣ ሦስት ሲኖትራክ፣ አንድ ኤፍኤስአር እና አንድ የቤት አውቶሞቢል መኪና ውስጥ የነበሩ እንደሆኑ ዋዜማ ተረድታለች። ከተሳፋሪዎቹ መካከል ሁለት ሰዎች ሸሽተው ማምለጣቸውን፣ ቀሪዎቹ ግን ይህ ዘገባ እየተጠናቀረ እስካለበት ሰዓት ድረስ በታጣቂ ቡድኑ እገታ ስር እንዳሉ የዐይን እማኞች ለዋዜማ አስረድተዋል።

          ጉጂ

    በክልሉ ምዕራብ ጉጂ ዞንም፣ በመንግሥት ወታደሮች እና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ በሚጠራው ታጣቂ መካከል ካለፈው ሰኞ ጀምሮ ግጭት ሲካሄድ መሰንበቱን ዋዜማ ከአካባቢው ያሰባሰበችው መረጃ ያመለክታል። ውጊያው በተለይም በዞኑ ሱሮ እና አበያ በሪን በመሳሰሉ ወረዳዎች እየተካሄደ መሆኑን የገለጹት ምንጮች፣ ከእነዚህ ወረዳዎች ወደ ዞኑ ዋና መቀመጫ ቡሌ ሆራ ከተማ ለመሄድ አለመቻላቸውንም ነግረውናል። ይህ ዘገባ እየተጠናከረ ባለበት ሰዓት፣ በአካባቢው ያለው ሁኔታ በአንጻራዊነት የተረጋጋ መሆኑን ዋዜማ የደረሳት መረጃ ያመለክታል። [ዋዜማ]

የአዘጋጁ ማስታወሻመረጃዎቹ አስከ ሰኔ 6 ቀን2016 ድረስ ብቻ ያለውን ሁኔታ የሚያንፀባርቁ መሆናቸውን ልብ እንድትሉልን እናስታውሳለን።

The post ኦነግ ሸኔ አዲስ ዘመቻ ጀምሯልን? first appeared on Wazemaradio.

The post ኦነግ ሸኔ አዲስ ዘመቻ ጀምሯልን? appeared first on Wazemaradio.

Source:: https://wazemaradio.com/%E1%8A%A6%E1%8A%90%E1%8C%8D-%E1%88%B8%E1%8A%94-%E1%8A%A0%E1%8B%B2%E1%88%B5-%E1%8B%98%E1%88%98%E1%89%BB-%E1%8C%80%E1%88%9D%E1%88%AF%E1%88%8D%E1%8A%95/?utm_source=rss&utm_medium=rss&utm_campaign=%25e1%258a%25a6%25e1%258a%2590%25e1%258c%258d-%25e1%2588%25b8%25e1%258a%2594-%25e1%258a%25a0%25e1%258b%25b2%25e1%2588%25b5-%25e1%258b%2598%25e1%2588%2598%25e1%2589%25bb-%25e1%258c%2580%25e1%2588%259d%25e1%2588%25af%25e1%2588%258d%25e1%258a%2595

Categories

A sample text widget

Etiam pulvinar consectetur dolor sed malesuada. Ut convallis euismod dolor nec pretium. Nunc ut tristique massa.

Nam sodales mi vitae dolor ullamcorper et vulputate enim accumsan. Morbi orci magna, tincidunt vitae molestie nec, molestie at mi. Nulla nulla lorem, suscipit in posuere in, interdum non magna.