መስፍን ወልደ ማርያም
መጋቢት 2012
የኢትዮጵያ ሕዝብ በእግዚአብሔር የሚያምን ነው፤ መናፍቃን የሉበትም ማለቴ አይደለም፤ የዘንድሮው ወረርሽኝ ግን መናፍቃኑን የበዙ አድርጓቸዋል፤ በዚህም የተነሣ በእግዚአብሔር ማመንና መተማመን ከወርሽኙ ጋር ፊት ለፊት የተፋጠጡ ይመስላል፤ ወረርሺኙን መፍራት እግዚአብሔርን ችላ ማለት፣ እግዚአብሔርን መፍራት ወረርሺውን ችላ ማለት እየመሰለ ነው፤ ‹‹እስመ አልቦ ነገር ዘይሰአኖ ለእግዚአብሔር›› የሚለውን ያመነ ለቫይረሱ ተገዝቶ ከቤተ እግዚአብሔር አይቀርም፤ ቫይረሱ በበኩሉ ‹‹ብታምንም ባተምንም እኔ አልምርህም፤›› ካለ እምነትና ቫይረስ ተፋጠጡ! ሀኪሞች እምነቱን ሳያድኑ ወረርሺኙን ማዳን ይችላሉ ወይ? ሊቃነ ጳጳሳቱስ ወረርሺኙን ሳያድኑ እምነታቸውን ማዳን ይችላሉ ወይ? ሀኪሞቹና ሊቃነ ጳጳሳቱም የተፋጠጡ ይመስላል!