Categories

A sample text widget

Etiam pulvinar consectetur dolor sed malesuada. Ut convallis euismod dolor nec pretium. Nunc ut tristique massa.

Nam sodales mi vitae dolor ullamcorper et vulputate enim accumsan. Morbi orci magna, tincidunt vitae molestie nec, molestie at mi. Nulla nulla lorem, suscipit in posuere in, interdum non magna.

በአማራ ክልል በእርግጥ መረጋጋት እየመጣ ነውን?

ዋዜማ – በአማራ ክልል በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የሚደረጉት ውጊያዎች፣ አሁንም ተባብሰው መቀጠላቸውን ዋዜማ በኹሉም የክልሉ አካባቢዎች ባደረገችው ማጣራት ተገንዝባለች።

ዐሥር ወራትን ባስቆጠረው የኹለቱ አካላት ግጭት በክልሉ የሚገኙት አብዛኞቹ የዞን እና የወረዳ ከተሞች በመንግሥት ወታደሮች ቁጥጥር ስር ሲሆኑ፣ የከተሞቹን ዙሪያ ጨምሮ ብዙዎቹ የገጠር ቀበሌዎች ደግሞ በታጣቂዎች እጅ መሆናቸውን ተረድተናል። ያሰባሰብናቸውን መረጃዎች ለንባባችሁ ይመች ዘንድ እንደሚከተለው ከክልሉ ከተሞች አኳያ አሰባጥረናቸዋል።

ጎንደር

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ታች አርማጭሆ እና ቆላድባ ወረዳዎች፣ በዚህም ሰሞን ውጊያ እንደነበር ዋዜማ ተገንዝባለች። በዚህም በቆላድባ ወረዳ ከጎንደር ከተማ በቅርብ ዕርቀት ላይ በምትገኘው ግራርጌ ቀበሌ፣ ከትናንት በስቲያ ከሰዓት ኹለቱ ኃይሎች የተኩስ ልውውጥ ሲያደርጉ ውለዋል። 

ከጎንደር ከተማ በቅርበት በምትገኘው ማክሰኝት ከተማ ዙሪያም ከትናንት በፊት ውጊያ ተካሂዷል ተብሏል። 

በምዕራብ ጎንደር ዞን ቋራ ወረዳ በተመሳሳይ፣ ከትናንት ወዲያ ሽንፋ በምትባል አነስተኛ የገጠር ከተማ ኹለቱ ኃይሎች ሲዋጉ እንደነበር ነዋሪዎች ለዋዜማ ገልጸዋል። 

ባለፈው ሳምንት ከዚህ ቀደም ውጊያ ተደርጎባቸው በማያውቁት አካባቢዎችም ተኩስ ነበር ያሉን አንድ ነዋሪ፣ አምባ ጊዮርጊስ በሚባል ቦታ በቅርቡ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና የፋኖ ታጣቂዎች ግጭት ውስጥ እንደነበሩ ገልጸዋል። 

ባለፈው ሳምንት በኹሉም የጎንደር ዞኖች በአብዛኛው መንገድ ተዘግቶ የነበረ ሲሆን፣ ከጎንደር ወደ ባህር ዳር እንዲሁም ከባህር ዳር ወደ ደብረታቦር የሚወስዱ መንገዶችም ታጣቂዎች ባስቀመጡት ክልከላ የተነሳ ዝግ ሆነው ሰንብተዋል። 

በደቡብ ጎንደር ዞን ደራ ወራዳ ባሉ ተራራማ ቦታዎችም፣ ሰኔ 5/2016 ዓ.ም. በከባድ መሳሪያ የታገዘ ውጊያ መቀስቀሱንም ከነዋሪዎች ሰምተናል። ግጭቱን ተከትሎም የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ወደ ወረዳው የተለያዩ ቀበሌዎች በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸው ታውቋል። 

ጎጃም

ባለፈው ሳምንት ብቻ በምዕራብ ጎጃም ዞን በቋሪት ወረዳ፣ በደጋ ዳሞት እና በደንበጫ በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች መካከል ውጊያዎች እንደነበሩ ዋዜማ ስምታለች።

የፋኖ ታጣቂዎች በአብዛኛው የሚከተሉት የውጊያ ስልት የሽምቅ ውጊያ ነው የተባለ ሲሆን፣ የመንግሥት ወታደሮች ቅኝት በሚያደርጉበት እና ስንቅ በሚያጓጉዙበት ወቅት ታጣቂዎቹ ተኩስ እንደሚከፍቱ ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል። 

በኹለቱ አካላት መካከል እየተካሄደ ያለው ግጭት ባላባራበት ቋሪት ወረዳ፣ የመንግሥት ሠራተኞች ደሞዝ ከተቋረጠ ከኹለት ወር በላይ እንደሆነውም ተገልጿል። 

በሰሜን ጎጃም ዞን አንድ የጎንጅ ቆለላ ወረዳ ነዋሪ፣ ከሳምንት በፊት የመንግሥት አካላት ወረዳዋ ዋና ከተማ ሕዝብ ሰብሰበው ግብር እንዲከፍሉ እያወያዩ በነበረበት ወቅት የፋኖ ታጣቂዎች ድንገት ደርሰው ተኩስ መክፈታቸውን ለዋዜማ ተናግረዋል። ከዚያ በኋላ በከተማዋ የዘፈቀደ እስር እና በሰላማዊ ሰዎች ላይ በመንግሥት የጸጥታ አካላት የሚደርሰው አካላዊ ድብደባ መጨመሩን ነዋሪው ነግረውናል። ከዋና ከተማዋ ወደ ባህር ዳር ለመሄድ 30 ብር የነበረው የትራንስፖርት ክፍያም እጅጉን ንሮ 200 ብር መድረሱን ነግረውናል። በወረዳው ትምህርት ቤቶችም አመቱን ሙሉ ዝግ እንደሆኑ ሰንብተዋል። 

በዞኑ በምትገኘው መራዊ ከተማ አቅራቢያም በቅርቡ በመንግሥት ወታደሮች እና በታጣቂዎች መካከል ከባድ ውጊያዎች ሲካሄዱ እንደነበር ነዋሪዎች ተናግረዋል። 

በምስራቅ ጎጃም ዞንም በኹለቱ ኃይሎች መካከል በየጊዜው ውጊያዎች እንደሚካሄዱም ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።

ያለፉትን ሁለት ቀናት ከደብረ ማርቆስ በቅርብ ዕርቀት ላይ ባለች የገጠር ቀበሌ፣ በኹለቱ ኃይሎች መካከል ውጊያ መኖሩንም ሰምተናል። ከሳምንት በፊት በዞኑ በሚገኘው ደጀን ወረዳ ጉብያ በምትባል አስነስተኛ የገጠር ከተማ፣ በኹለቱ ኃይሎች መካከል በነበረ የተኩስ ልውውጥ በትንሹ ሰባት ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውንም የዓይን ዕማኞች ገልጸዋል።

ከደጀን ወረዳ ወደ ዞኑ ዋና ከተማ ደብረማርቆስ በሚወስደው አውራ ጎዳና ላይ፣ የፋኖ ታጣቂዎች በትንሹ ኹለት ኬላ ዘርገተው ፍተሻ እንደሚያደርጉ ነዋሪዎቹ መስክረዋል። ሆኖም ከደጀን ደብረማርቆስ ለመጓዝ የጸጥታ ችግሩ ከመፈጠሩ በፊት 70 ብር ያስፈልግ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ላይ 300 እና 400 ብር ደርሷል ተብለናል፤ ተቆጣጣሪ አካል ባለመኖሩ አሽከርካሪዎች የፈለጉትን የዋጋ ተመን ያወጣሉም ነው የተባለው። 

አንድ የሞጣ ከተማ ነዋሪ ደግሞ፣ ከሳምንት በፊት ከከተማው ወጣ ብለው በሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች ውጊያዎች እንደነበሩ ገልጸው፣ በከተማዋ ትምህርት ቤቶች ዓመቱን ሙሉ ዝግ ሲሆኑ፣ ጤና ተቋማትም የመድኅኒት እና የህክምና ቁሳቁስ እጥረት እንዳለባቸው ይገልጻሉ። ከሞጣ ባህርዳር በመኪና ለመጓዝ የሰላም ችግር ከመፈጠሩ በፊት የነበረው ታሪፍ 80 ብር ቢሆንም፣ አሁን ወደ 500 ብር ማሻቀቡ ተሰምቷል።

ከሞጣ ባህር ዳር ባለው የመኪና መንገድ በትንሹ ሦስት የፋኖ ታጣቂዎች ያቋቋሙት የፍተሻ ጣቢያ ያለ ሲሆን፣ ኹሉም መኪኖች ቀረጥ ለመክፈል ይገደዳሉ ተብሏል። በዚሁ መንገድ ሰው የሚያመላልሱ ተሽከርካሪዎች በቀን 500 ብር ለቀረጥ የሚከፍሉ ሲሆን፣ እህል እና ሸቀጥ የጫኑ መኪኖችም የተለያየ የገንዘብ መጠን የመክፈል ግዴታ ተጥሎባቸዋል።

በእነዚህ እና በሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች ሸቀጦች ከፍተኛ የዋጋ ጭማሬ ታይቶባቸዋል ፣ በኹሉም የጎጃም አካባቢዎች መንግሥት የጣለው ግብር ከፍተኛ ነው የሚል ቅሬታ መኖሩንም ሰምተናል። ለአብነትም ከደብረማርቆስ እና ሞጣ ከተሞች ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች፣ ባለፈው ዓመት 10 ሺህ ብር የከፈሉ ነጋዴዎች፣ ዘንድሮ እስከ 50 ሺህ ብር እንደተጣለባቸው ነግረውናል። በብዙ ቦታዎች ግን መንግሥት የጣለው ግብር እንዳልተሰበሰበ ዋዜማ ተረድታለች።  

ወሎ

በወሎ የተለያዩ አካባቢዎችም በኹለቱ አካላት መካከል ውጊያዎች ሲካሄዱ ነበር የተባለ ሲሆን፣ ለአብነትም በደቡብ ወሎ ዞን ቦረና ወረዳ ባለፈው ቅዳሜ የመከላከያ ሠራዊት አባላትን ጭኖ በነበረ ተሽከርካሪ ላይ ታጣቂዎቹ ባደረሱት ጥቃት የተነሳ የተኩስ ልውውጥ ሲደረግ እንደነበር በአካባቢው ያሉት ነዋሪዎች ነግረውናል።  

ከባለፈው ሳምንት መጨረሻ ጀምሮም በመሃል ሳይንት፣ አማራ ሳይንት፣ መቅደላ እና ወግዲ ወረዳዎች ተመሳሳይ የተኩስ ልውውጦች ነበሩ ።

ሰኔ 5/2016 ዓ.ም. በሰሜን ወሎ ዞን ወደምትገኘው ቆቦ ከተማ ዙሪያ የፋኖ ታጣቂዎች መጠጋታቸውን ተከትሎ በነዋሪዎች ዘንድ ስጋት ተፈጥሯል። በከተማው ውስጥ የመከላከያ ሠራዊት ዲሽቃ በጫኑ ፓትሮሎች እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ የዓይን ዕማኞች ገልጸዋል።  በዞኑ በምትገኘው ሀብሩ ወረዳም ሰኞ ዕለት የፋኖ ታጣቂዎች እና የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ሲዋጉ ውለዋል ተብሏል። 

በደቡብ ወሎ ዞን በተመሳሳይ ከደሴ ወደ ወልዲያ በሚወስደው መንገድ ላይ በሚገኘው የአምባሰል ወረዳ ውጫሌ እና ሮቢት በሚባሉት አካባቢዎችም፣ ባለፈው ሰኞ ዕለት በኹለቱ ኃይሎች መካከል ውጊያ እንደነበር ነው ነዋሪዎች ተናግረዋል። በዕለቱ በተለሁድሬ ወረዳ ሐይቅ ከተማ ዙሪያ ተኩስ ነበር ያሉት ነዋሪዎቹ፣ በእነዚህ አካባቢዎች ሰሞኑን በነበረው ውጊያ ቁጥራቸው በርከት ያሉ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውንም ገልጸዋል። 

አንድ የደሴ ከተማ ነዋሪ፣ ‘ማታ ማታ የወታደር ልብስ ለብሰው እና ታርጋ የሌለው መኪና ይዘው በሚመጡ ሰዎች፣ ከቤታቸው ታግተው ተወስደው በመቶ ሺሕዎች የሚጠየቁ ሰዎች በጣም በርካታ ናቸው’ ብለውናል። ከተወሰዱ በኋላ ከፍተኛ ድብደባ የሚፈጸምባቸው መኖራቸውንም አክለዋል። 

በወሎ በሚገኙ የመኪና መንገዶች ላይም የፋኖ ታጣቂዎች ኬላ አቋቁመው ፍተሻ እንደሚያደርጉ እና በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ቀረጥ እንደሚያስከፍሉ ዋዜማ ተገንዝባለች። 

ሸዋ

በሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥም ባለፈው ሳምንት እና በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ቀናት፣ በተለያዩ አካባቢዎች ውጊያዎች ሲደረጉ እንደነበር በአካባቢው የሚገኙ ነዋሪዎች ገልጸዋል። 

ለአብነትም በመኮይ፣ ኤፍራታ ግድም እና ሌሎች ወረዳዎችም የመንግሥት ወታደሮች ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር ሲታኮሱ ነበር ተብሏል።

እንዲሁም በመርሓ ቤቴ፣ መንዝ ሞላሌ እና ምንጃር አካባቢዎች ሰሞኑን ተመሳሳይ ግጭቶች ተካሂደዋል። 

በዞኑ ብዙ ቦታዎች አልፎ አልፎ የሚደረጉ የተኩስ ልውውጦች በየቀኑ የተለመዱ ናቸውም ተብሏል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ በክልሉ ባለው የጸጥታ ችግር እንዲሁም ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ባለውም የመንገደኞች እገታ ምክንያት ከጎጃም እና ጎንደር ወደ አዲስ አበባ የሚደረግ የመንገደኞች ጉዞ ከቆመ ብዙ ጊዜ ሆኖታል ። በዋናነት የመከላከያ ሠራዊት አባላትን ጭነው ከአዲስ አበባ ወደ አማራ ክልል የሚገቡ መኪኖችን ጠብቀው የሚመላለሱ አንዳንድ የሕዝብ ማመላለሻ መኪኖች መኖራቸውን ነዋሪዎች አመልክተዋል።  

በኹለቱ ኃይሎች መካከል በየጊዜው የሚፈጠሩት ግጭቶች፣ በአብዛኛው በሰላማዊ ሰዎች ላይ ሞት እና የአካል ጉዳት እንደሚያስከትሉም ነዋሪዎች ገልጸዋል።  

በክልሉ ኹሉም አካባቢዎች ሰላም ከመደፍረሱ በፊት የነበረው የትራንስፖርት ክፍያ ሦስት እና አራት ዕጥፍ መጨመሩም በነዋሪው ላይ ከባድ ጫና እየፈጠረ መሆኑን ኹሉም ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ገልጸውልናል። እንዲሁም የገበሬዎች ሰብል በኹለቱም ኃይሎች አማካኝነት ጉዳት እንደሚደርስበት እና ለፋኖ ወይም ለመከላከያ እንስሳት ሽጣችኋል፣ እህል አብልታችኋል፣ ጥቆማ ሰጥታችኋል ወዘተ በሚሉ ምክንያቶች ኹለቱም ወገኖች ሰላማዊ ሰዎች ላይ ሞት እና የአካል ጉዳት እንደሚያደርሱ ነዋሪዎቹ መስክረዋል። 

በየአካባቢዎቹ በተለይ የግል ባንኮች ለደንበኞቻቸው የሚሰጡት ገንዘብም በጣም ውስን ነው ተብሏል። 

በክልሉ ለአስር ወራት ተጥሎ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ባለፈው ግንቦት 28 የጊዜ ገደቡ ተጠናቋል። [ዋዜማ]

የአዘጋጁ ማሳሰቢያይህ ዘገባ እስከ ሰኔ ቀን ብቻ ያሉትን መረጃዎች ያካተተ መሆኑን ልብ እንድትሉልን እናስታውሳለን።

The post በአማራ ክልል በእርግጥ መረጋጋት እየመጣ ነውን? first appeared on Wazemaradio.

The post በአማራ ክልል በእርግጥ መረጋጋት እየመጣ ነውን? appeared first on Wazemaradio.

Source:: https://wazemaradio.com/%E1%89%A0%E1%8A%A0%E1%88%9B%E1%88%AB-%E1%8A%AD%E1%88%8D%E1%88%8D-%E1%89%A0%E1%8A%A5%E1%88%AD%E1%8C%8D%E1%8C%A5-%E1%88%98%E1%88%A8%E1%8C%8B%E1%8C%8B%E1%89%B5-%E1%8A%A5%E1%8B%A8%E1%88%98%E1%8C%A3/?utm_source=rss&utm_medium=rss&utm_campaign=%25e1%2589%25a0%25e1%258a%25a0%25e1%2588%259b%25e1%2588%25ab-%25e1%258a%25ad%25e1%2588%258d%25e1%2588%258d-%25e1%2589%25a0%25e1%258a%25a5%25e1%2588%25ad%25e1%258c%258d%25e1%258c%25a5-%25e1%2588%2598%25e1%2588%25a8%25e1%258c%258b%25e1%258c%258b%25e1%2589%25b5-%25e1%258a%25a5%25e1%258b%25a8%25e1%2588%2598%25e1%258c%25a3

Categories

A sample text widget

Etiam pulvinar consectetur dolor sed malesuada. Ut convallis euismod dolor nec pretium. Nunc ut tristique massa.

Nam sodales mi vitae dolor ullamcorper et vulputate enim accumsan. Morbi orci magna, tincidunt vitae molestie nec, molestie at mi. Nulla nulla lorem, suscipit in posuere in, interdum non magna.